Skip to main content
001

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከሦስት ዞኖች ጋር የሚያካሂደው የጋራ የፀጥታ ጥምረት የግምገማ መድረክ በዱራሜ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከከምባታ፣ ከሀዲያ እና ከሀላባ ዞኖች ጋር በመተባበር በአካባቢዎቹ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ የሚያተኩር የጋራ የፀጥታ ጥምረት የግምገማ መድረክ በዱራሜ ከተማ እያካሄደ ይገኛል። 

ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር የገባው ይህ የጋራ የፀጥታ ጥምረት የመንገድ ላይ ወንጀሎችን መመከት የሚያስችል ዕቅድ አቅዶ ፣ በአካባቢው አስተማማኝ የሰላም ለውጥ ማምጣቱን መድረኩን የመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ የገለጹ ሲሆን፤ የዛሬው ውይይትም በዋናነት በሦስቱ ዞኖች አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ የሚታዩ አሁናዊ ሁኔታዎችን እና የፀጥታ ስጋቶችን በጥልቀት ለመገምገም የተዘጋጀ መሆኑንም አንስተዋል። ውይይቱ በተለይም ስርቆትን፣ ዝርፊያን እና ሌሎች ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል ዙሪያ ከየዞኖቹ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑም ተመላክቷል። 

የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎልና የሕዝብ ንብረት እንዳይወድም ለማድረግ፤ እንዲሁም ጽንፈኛ ኃይሎች የሚፈጥሩትን እኩይ የጥፋት ሴራ ቀድሞ ለማክሸፍ የሁሉም አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሷል። የአካባቢውንና የክልሉን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩና ማኅበረሰቡ የነቃ የሠላም እንቅስቃሴና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም በውይይቱ ተነስቷል። 

መድረኩን በክልሉ ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ እየመሩት ሲሆን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል እና ትራፍክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብርሃም ቲርካሶ፣ የክልሉ ሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ተሻለ ኤርዲዶ ጨምሮ የከምባታ፣ የሀዲያ እና የሀላባ ዞኖች የፀጥታ ኃላፊዎች የሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ፣ የፖሊስ አዛዦች እና የአዋሳኝ ወረዳ የፀጥታ አካላት ተገኝተዋል።